የመጋቢው መልዕክት

pastorበዚች ምድር የሰው ልጅ በሙሉ ከመጀመሪያው አዳም በሐጥያት ውድቀት የተነሳ በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖር አልተፈቀደለትም። የምድር ቆይታው የተወሰነ ነው። ምኞታቸውንና ተስፋቸውን ከምድር ጋር ካጣበቁና “ምድር ገነት ትሆናለች ስለዚህ በምድር ለዘላለም እንኖራለን” ከሚሉ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ አመላካከትና አስተምሮ ካላቸው ግለሰቦችና የሐይማኖት ድርጅቶች በስተቀር እውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል አንድ ቀን ምድርና ከምድር የሆነው ሁሉ ተጠቅለው እንደሚያልፉ በግልጽ ይናገራል።

ማንኛው ሰው በክርስቶስ አመነም አላመነም በምድር ላይ እንዲኖር የተቀጠረለትንና የተወሰነለትን እድሜውን ከፈጸመ በኋላ ፍጻሜና ማብቂያ ወደሌለበት ዘላለማዊ ህይወት ይሸጋገራል (በመንግስተ ሰማይ ይም ደግሞ በገሃነም)። ሰው ቢቀበለውም ባይቀበለውም ይህንን እውነት ሊለውጠው አይችልም።

ቃሉ “ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው” (ዕብራውያን 9. 27) በማለት ሰው በምድር ፍጻሜ እንዳለው አጥብቆ ያሳስበናል። ሰው በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን የዘላለም ህይወት ቢያገኝ ለዘላለም አስደናቂ ሰላምና እረፍት እንዲሁም ፍጹም ደስታ በተሞላበት ሁኔታ በማይሰለች የዘላለም ህይወት ውስጥ ካመነው ጌታ ጋር ይኖራል። በተቃራኒው ይህንን ለእርሱ ሲል በመስቀል ላይ የሐጥያቱን ዋጋ ለመክፈል የሞተለትን የእግዚአብሔርን ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመቀበል በእምቢተኝነት ቢመላለስ የእርሱም የምድር እድሜ ያበቃና ፍጻሜ የሌለው ስቃይና ጥርስ ማፏጨት ያለበት የዘላለም እሳት ይጠብቀዋል። እንግዲህ ከሁለቱ አንዱን የመምረጥ ዕድሉ ያለው ለአጭር ጊዜ በሚኖርባት በዚህች ምድር ላይ ብቻ ነው።

ይህ ሁሉ ሊያበቃ ጌታም እንደገባው የተስፋ ቃል ሙሽራው የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን ሊወስድ በደጅ ነው። ስለዚህ ለእኛ ጌታን ለተቀበልነው ለያንዳንዳችን ትልቁ ነገር ይህንን አውቀንና ተገንዝበን ያለንበትን ዘመን በመመርመር ዘመኑን እየዋጀን(እየተጠቀምንበት) በክብር፤በግርማ በብዙ መላዕክትና በብዙ የመለከት ድምጽ በመታጀብ የሚመለሰውን ጌታ መጠባበቅ ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ዝንጉዎች በቀደሙት በአባቶች ዘመን እንደነበሩ ሁሉ በዚህም ባለንበት በእኛም ዘመን እንደ አሸን እየፈሉ እንድዳሉ እውነት ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ እነዚህ ዝንጉዎች እንዲህ በማለት ጽፎአል። “

“በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እርሱም፦ የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፥ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ።” (2ኛ ጴጥ. 3. 3-4)

ስለዚህ በዘመናችንም እርሱ አይመጣም ወይም መጥቷል የሚሉ ዘባቾች ቢነሱም አዲስ አይደለም። ይሁን እንጂ ህያው የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ እንደሚናገረው “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።” (2ኛ ጴጥ.3.9)

ጌታ አይመጣም ምድር እንዳለች ለዘላለም ትኖራላች ለሚሉም ከእግዚአብሔር ቃል መልስ አለ፡ “ የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።” ( 2ኛ ጴጥ. 3.10 )

ለእኛ በጌታ ላለን ደግሞ የጌታ ቃል አበክሮ የሚመክረን ነገር ቢኖር በቅዱስ ኑሮ እየተመላለስን ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ በትግስት ሆነን የከበረ ተስፋችንን እንድንጣጥባበቅ ነው።

“ ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥ የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ። ” (2ኛ ጴጥ. 3. 12-15)

ወገኖቼ ሆይ እንድ እግዚአብሔር ባሪያ ላነቃቃችሁ የምፈልገው ነገር ቢኖር የእግዚአብሔርን ቃል በመኖር ዘመኑን እየመረመርንና ዘመኑ ሳይሆን እኛ በዘመኑ ላይ እየሰለጠንን የተሰጠንን የወንጌል አደራ በመወጣት በንቃትና በጉጉት ታላቁ ተስፋችን የሆነውን የጌታችንና የመድሃኒታችንን ዳግም መምጣት እንድንጠባበቅ ነው። ጌታ ከምንጊዜው በበለጠ ከድጅ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለነበሩት ቅዱሳን ስለመምጣቱ እንዲነቃቁና በጥንቃቄ ሆነው እንዲጠባበቁ እንዲህ እያለ ሲያበረታታቸው እንመለከታለን።

“ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጕዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም። እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፥ ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም፤ እንግዲያስ እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ።” 1ኛ ተሰ. 5. 1-6

እንዲሁም “ የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ፤ ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” (ዕብራውያን 10. 23-25) በማለት ለእኛም ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ ነቅተን እንድንኖር ያሳስበናል።

ስለዚህ ወገኖቼ ሆይ ጌታ ለመምጣት በደጅ ነው። ስለሆነም ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ የግላችንን ህይወት በእግዚአብሔር ቃል እየፈተሽን በእግዚአብሔር መንፈስ በመመራት እርስ በርሳችን እየተሳሰብንና በጌታ ዳግም መምጣት እየተጽናናን በክርስቶስ ሙሉ ሰው ወደ መሆን እያደግን ለሌሎችም ይህንን ነጻ የወጣንበትን ነጻ አውጪ የሆነውን የመንግስት ወንጌል በድፍረትና በቆራጥነት እያወጅን ወደ ክርስቶስ ህብረት እንድናመጣቸው ይጠበቅብናል። ለዚህ ደግሞ የጌታ ጸጋና ሞገስ ይረዳናል። ወደ ፊት የሚባክን ጊዜ ከፊት ለፊታን አይኖረንም። አንድ ቀን ብቻ የምድር ኑሮ እንደቀረው ሰው ዛሬን እንጠቀምብት በቸልታ ቀኑ አይለፈን።

የጌታ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ ጌታ ይመጣል ማራናታ!!!

መጋቢ ገበየሁ ፈለቀ

Comments are closed.